ስውር ውጊያ

Avatar By admin Feb 10, 2024

ተደጋጋሚና አሰልቺ የሆኑ የፍቅር ታርኮችን ብቻ የሚያዘወትረው የአማርኛ ፊልም ሰሞኑ አዲስ ዣንራን የቀላቀለ ይመስላል። መለኞቹ፣ ንስሮቹና ስውር ውጊያ የተሰኙ በደህንነትና የኢንተሊጀንስ ጒዳዮች ላይ የሚያተኲሩ ፊልሞች በኢትዮጵያ የፊልም ኢንዱስትሪ ውስጥ ብዙ ያልተለመዱ ዣንራዎች ናቸው ብየ አስባለሁ።

ስውር ውጊያ

ፊልሙ ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ የገንዘብ ተቋማትና የዓባይ ግድብ ላያ ያነጣጠረ የሳይበር ጥቃቶች ላይ የሚያተኲር ነው። ፊልሙ ሲጀምር ከሳይበር ደህንነት ጋር ብዙ ግንኙነት የሌላቸው በሚመስሉ ትይዕንቶች ነው። በኮምፕዩተር ላይ የሚያፈጥ አንድ ትንሽ ልጅ (በርግጥ የልጁ ፍላጐት የኮምፕዩተር ባለሙያ መሆን እንደሆነ ያሳያል)፣ የፍቅር ቀጠሮ ያለበት የሚጣደፍ ወንድ (የታደለ ወንድ ፍቅረኛውን ለመጋበዝ ከእናቱ ብር የሚቀበል)፣ በሥራ ምክንያት ተለያይተው የተነፋፈቊ ባለ-ትዳሮች (የድርጅት ኀላፊዎች ቢሮአቸው አጠገብ መኖሪያ ቤት ቢሰጣቸው አይከፋም፣ ሴት የላከችው ሞት አይፈራም በሚል ቢህል)፣ በታራቡ ሦስት እጆች ፊት የቀረበች አንዲት ብጣሽ እንጀራ. . . ወዘተ።

ኋላ ግን ሲታይ የእነዚያ ሁሉ ሕይወት በአንዲት የሳይበር ጥቃት ምክንያት ተመሰቃቀለ። ሕይወታችን ምን ያህል ከዲጅታል ዓለሙ አሠራር ጋር የተቆራኘ እንደሆነ ግልጽ ማሳያ ነው። የሳበር ጥቃቱ በተሳካ ሁኔታ ሁለት ተቋማትን፣ ማለትም ፕላኔት ኢንተርናሽናል ባንክ(ምናባዊ ባንክ) እና የዓባይ ግድብ ላይ እንደተፈጸመ ያሳያል። ‘እውነተኛ ሁኔቶች’ ላይ የተመሠረተ ነው ስለተባለ የአባይ ግድብ ሳናውቀው አደጋ ውስጥ ገብቷል ማለት ነው፣ ምስጋና ለዲጂታል ሠራዊት! የጥቃቱ ዓላማ ለአባይ ግድብ ሲሚንቶ የሚያመርተውን ፋብሪካ በማጥቃት Chemical composition እንዲቀየር በማድረግ፣ ከደረጃ በታች የሆነ ሲሚንቶ ተመርቶ በግድቡ ግንባታ ላይ የጥራት ችግር እንዲፈጠር በማድረግ፣ ከዚህ ጐን ለጐን ደግሞ ‘በግድቡ ጥራት ላይ ጥርጣሬ አለን’ በማለት ዓለም ዐቀፍ የጥራት ቊጥጥር ባለሙያዎች ለፍተሻ እንደመጡ ፖለቲካዊ ጫና መፍጠር ነበር። ጥራቱ በወረደው ሲሚንቶ የተገነባው ግድብ ከደረጃ በታች መሆኑ ስለማይቀር ባለሙያዎቹ ይደርሱበታል ማለት ነው፣ በዚህም የግድቡ ግንባታ  በዓለም ዐቀፍ ጫና ምክንያት እንዲቆም ወይም እንዲስተጓጐል ይደረጋል ማለት ነው። ዕቅዳቸው አልተሳካም፣ እንደ ደካማ የቆጠሩት የኢትዮጵያ የሳይበር ምህዳር በጠንካራ ሠራዊት እንደሚጠበቅ የተረዱት በጣም ዘግይተው ነው። ኢትዮጵያ ኋላ ቀር አገር ነች ብለው ብዙውን ጊዜ ድንበር ጥሰው ለትንኮሳ የመጡ ሁሉ አፍረው እንደተመለሱ ሁሉ፣ የሳይበር ድንበር ጥሰው በተከለከለው ድንበር የተገኙ ታሪካዊ ጠላቶች ባልጠበቊት መንገድ ተጠልዘው በመርፌ እንደተነካች ፊኛ ኩምሽሽ ብለዋል።

ግን እንደዚህ ዓይነት ጥቃቶች መፈጸም ይቻላል?

በኮምፕዩተሮች ወይም በሌሎች ዲጂታል ቁሳቁሶች ላይ የሚጫኑ መተግበሪያዎች በጸረ-መተግበሪያ(ቫይረስ) አማካይነት እንደሚበላሹ በአንድም በሌላም መንገድ ስንሰማ ኖረናል። ነገር ግን ክፉ መተግበሪያ (Malware) ተጠቅሞ አንድን ፋብሪካ ማጥቃት ይቻላል ወይ የሚለው ጥያቄ ሊያስነሳ ይችል ይሆናል። ይቻላል ወይስ አይቻልም የሚለውን ጥያቄ የሚመልስ ኢራን ውስጥ የተፈጸመ የሳብር ጥቃት ክስተት ማንሣት ተገቢ ይሆናል።

ኢራን የንኲልየር ግንባታ ታካሂዳለች ተብላ ትወቀስ ነበር። ምንም እንኳን ኢራናውያን ንኲለየሩን የሚሠራው ለልማት ነው ብትልም ሰሚ አላገኘችም። በመጨረሻ በ2010 ላይ Stuxnet የሚባል ክፉ መተግበሪያ አምርተው ወደ ናታንዝ ዩራኒየም ማበልጸጊያ ጣቢያ ይልካሉ። ትል (Worm) የሚባለው ክፉ መተግበሪያው የተላከው በፍላሽ ዲስክ ተደርጐ ነው። ምክንያቱ ደግሞ ጣቢያው ከየትኛውም የሳይበር ዓለም ጋር ምንም ግንኙነት ባለመፍጠሩ ነው (air gap) ። ስለዚህ ያለው አማራጭ የሰው ኤጀንት ተጠቅመው ፍላሹን አንድ ኮምፕዩተር ላይ መሰካት ነበር፣ አደረጒት። ትሉ (Worm) ዒላማ ድርጅቱ የፋብሪካውን እንቅስቃሴ የሚቆጣጠሩበት ‘ Siemens Step7 ’ የተባለ ሶፍትዌር ነው። ሶፍትዌሩ ከተጠቃ በኋላ ማሽኖችን የሚያንቀሳቀስበት ፍጥነት በብዙ እጥፍ በመጨመር (supersonic speed) በራሳቸው ጊዜ ተቃጠለው ከጥቅም ውጪ እንድሆኑ ማድረግ ነው። እንደ ካስፐረስኪ(Kaspersky) መረጃ ጥቃቱ ከ200,000 ኮምፕዩተሮችና ከ1000 በላይ የፋብሪካውን ማሽኖች ከጥቅም ውጪ አድርጓል። ይኸ ክፉ መተግበሪያ የዓለማችን የመጀመሪያ “ዲጂታል ቦምብ” ተብሎ ተጠርቷል። ከኮምፕዩተሮች አልፎ ኤሌክትሮ-መካኒካል የሆኑ ቊሶችም ጭምር የሳይበር ጥቃት ሰለባ ሊሆኑ እንደሚችሉ ለዓለም ትልቅ ማስተማሪያ ሆኗል።

ስለዚህ የዓባይ ግድብን በዲጂታል ቦንብ ማጥቃት መሞከር ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል ስለሚያወቊ ለመጠቀም ሞክረዋል። እነ ትራምፕ ግብጽ ግድቡን ልታጋየው ትችላለች ያሉት ምናልባት በዚህ በዲጂታል ቦንብ ሊሆን ይችላል።የፊልሙ ስክርፕት የጻፈው ሰው ይኸንን ታሪክ እንደ መነሻ የተጠቀም ይመስላል፣ ታሪኩ ስለሚመሳሰል።

ትንሽ የተንዛዛ የመግቢያ Footages አሉት። ምክንያቱም ፊልሙ የሚጀምረው በአገር ውስጥ ያሉ የተለያዩ ተቋማት አሠራር የሚያሳዩ ክሊፖችን ለ5 ደቂቃዎች ካሳየ በኋላ ነው። ሌላው ጥቃቱን የለዩበት ፍጥነት ከእውነተኛው የሳይበር ጥቃት የተለየ ይመስላል። ምናልባት ጥቃት አድራሾቹ በቴክኒካል ቋንቋ ‘Script kiddies ናቸው እንዴ’ እንድንል ያደርገናል። የሀክንጒን ተግባር የወከሉ ገጸ-ባህሪያት እንደነ Nmap ያሉ መሣሪያዎችን (Tools) ቢጠቀሙ የበለጠ ያምር ነበር፣ በብዛት በዚህ ርዕስ ላይ የተሠሩ ፊልሞች ይጠቀሙታል። የ Malware ዓይነት ምንድን ነው? ስም ቢሰጡት ጥሩ ነበር።

Avatar

By admin

Related Post