እውነተኛ የሥራ ግንዛቤ በክርስቲና ክፍል ፮

Avatar By Guwad K. Mar 31, 2024

በመጽሐፍ ቅዱስ እይታ

ክርስቲያናዊ ሥነ-ምግባሮች የሚቀዱት ከመጽሐፍ ቅዱስ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሥራ ምን እንደሚያስተምር ማየት ትክክለኛውን መልዕክት ለማየት ይረዳናል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የሰው ልጅ ከተፈጠረበት ጊዜ አንስቶ አሁን እስካለበት ጊዜ ድረስ የተከናወኑ ዐበይት ክንውኖችን በሦስት ደረጃዎች ከፍለን ለማየት እንሞክራለን፡፡

የሰው ልጅ ከውድቀት በፊት

በሥነ መለኮት ትምህርት ውድቅት የሚባል ታሪክ አለ፡፡ የሰው ልጅ የተፈጠረው በእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ ነው፡፡ ሆኖም ግን ሰው በተፈጠረበት ማንነት እስከ መጨረሻ ድረስ መጽናት ባለመቻሉ የተከለከለውን አድርጎ በኃጢአት ወደቀ፡፡ በዚህም ከአምላኩ ጋር ተጣላ፣ መልካም ከሆነችው ገነት ተባረረ፡፡ የአንድ ሰው ኃጢአት መሥራት ዓለም ሁሉ በሱ ምክንያት እንድትረገም ምክንያት ሆነ፡፡ ይህ ነው ውድቀት ማለት፣ የሰው ልጅ ኃጢአት በማድረጉ ምክንያት ከአምላኩ ጋር የተጣላበት ክስተት ነው፡፡

አዳምንም አለው፦ የሚስትህን ቃል ሰምተሃልና፥ ከእርሱ እንዳትበላ ካዘዝሁህ ዛፍም በልተሃልና ምድር ከአንተ የተነሣ የተረገመች ትሁን፤ በሕይወት ዘመንህም ሁሉ በድካም ከእርስዋ ትበላለህ፡፡ 

ኦሪተ ዘፍጥረት ምዕራፍ 3 ቁጥር 17                                              

ታሪኩ ግን በዚህ ብቻ አይደመደምም፡፡ እግዚአብሔር የሳተውን ሰው ለመመለስ ብዙ ጥረቶችን ሲያደርግ ቆይቶ በመጨረሻ አንዲያ ልጁን ልኮ በሰው ልጆች ኃጢአት ፈንታ እንዲሞት አደረገ፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ በመሞቱ በኃጢአት ምክንያት ከአምላኩ ጋር የተጣለው የሰው ልጅ እንደገና እርቅ አደረገ፡፡ ይህ በሥነ መለኮት ቋንቋ ቤዛነት ይባላል፡፡

ስለዚህ ስለ ሥራ ከመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ ጋር ከነዚህ የሰው ልጅ ክስተቶች ጋር አያይዞ ማየት የበለጠ ግልጽ ይሆናል፡፡

ሥራ ከውድቀት በፊት

ለመሆኑ የሰው ልጅ ኃጢአት ሠርቶ ከገነት ከመባረሩ በፊት ሥራ ይሠራ ነበር? አንዳንድ ሰዎች ሥራ ከእርግማን የተነሣ በሰው ልጆች ላይ የተጣለ ቅጣት እንደሆነ ያስባሉ፡፡ ይህንን አስተሳሰብ ትክክል ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ለመረዳት ከውድቀት በፊት የነበረው የሰው ልጅ ምን ይሠራ እንደነበረ ወይም የተሰጠው ኃላፊነት ምን እንደሆነ እዚያው በዘፍጥረት መጽሐፍ ማግኘት እንችላለን፡፡ አንደኛ ሰውን የፈጠረው አምላክ ራሱ ሥራን እንዴት እንደሚያይ ማየቱ ተገቢ ነው፡፡

እግዚአብሔር ሠራተኛ ነው

መጽሐፍ ቅዱስ ከፍቶ የመጀመሪያውን ምዕራፍ ያነበበ ሰው እግዚአብሔር ምን ዓይነት አምላክ እንደሆነ ይገነዘባል፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያው ምዕራፍ “በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ” ብሎ ይጀምራል፡፡ መፍጠር ሥራ ነው፣ ስለዚህ እግዚአብሔር ከኛ ጋር የሚተዋወቀው በሥራ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር ሠራተኛ እንደሆነ ያሳያል፡፡ መፍጠር፣ ከሕዝብ ጋር ቃል ኪዳን መግባት፣ ቤዛዎት፣ ወዘተ… የእግዚአብሔር ሥራዎች ተደርገው ይቆጠራሉ፡፡ እያንዳንዱን ፍጥረት መደገፍ፣ ማስቀጠልና (Sustain ማድረግ) መመገብ የፈጣሪ ሥራ ነው፡፡

አዳም ሥራ ነበረው

ከውድቀት በፊት የነበረው አዳም እንዲሁ ተዝናንተህ ብላ አልተባለም፡፡ ይልቁን ከእግዚአብሔር ጋር ሆኖ ሥራ ላይ ሲሳተፍ እንመለከታለን፡፡

“እግዚአብሔር አምላክም የምድር አራዊትንና የሰማይ ወፎችን ሁሉ ከመሬት አደረገ፤ በምን ስም እንደሚጠራቸውም ያይ ዘንድ ወደ አዳም አመጣቸው፤ አዳምም ሕያው ነፍስ ላለው ሁሉ በስሙ እንደ ጠራው ስሙ ያው ሆነ።” ዘፍ. 2፡19

እዚህ ቦታ ላይ አዳም በፈጣሪው ሥራ ሲሳተፍ እንመለከታለን፡፡ እግዚአብሔር ፈጥሮ እንደጨረሰ ለእንስሳት ሁሉ ስም አውጥቶ ወደ አዳም አምጥቶ ስማቸውን እንዲሸመድድ ማድረግ አይችልም ነበር? ይችላል፡፡ ነገር ግን አዳምም የሥራው ተባባሪ መሆን ስለፈለገ አሳተፈው፡፡

ሌላው ወሳኝ ሐሳብ የምናገኘው ዘፍጥረት ምዕራፍ 2 ላይ ነው።

“…እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ወስዶ ያበጃትም ይጠብቃትም ዘንድ በዔድን ገነት አኖረው።”

ይህ ሐሳብ አዳም እግሩን ዘርግቶ የሚበላ ለሚመስቸው በቂ ማስረጃ ነው፡፡ ማበጀትና መጠበቅ ትልቅ ኃላፊነት ነው፡፡

ከላይ እንደተመለከትነው ሥራ በእርግማን ምክንያት በሰው ላይ የወረደ መዓት ሳይሆን የሰው ልጅ የተፈጠረለት ዓላማ ነው፡፡ አዳም በኃጢአት ባይወድቅ እንኳን ሥራ መሥራት እንደሚኖር በበቂ ሁኔታ መገንዘብ ይቻላል፡፡

ሥራ ከውድቀት በኋላ

ደግሞ ከእናንተ ጋር ፦ሊሠራ የማይወድ አይብላ ብለን አዘናችሁ ነበርና።

2ኛ ተሰሎንቄ 3፡10

ከላይ የተጠቀሰው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ እንደሚያመለክተው ከውድቀት በኋላ መሥራትና መብለት በቀጥታ መያያዛቸው ነው፡፡ ከውድቀት በፊት ሥራና መብላት የሚገናኙ አልነበሩም፣ አዳም ቢሠራም ባይሠራም መብላቱ አይቀርም ነበር፡፡ ሥራ ኃላፊነት የተሰጠው እንጂ የሚበላውን ለማምረት የሚያደርገው ጥረት አልነበረም፡፡ ከውድቀት በኋላ ግን ሥራና መብላት በቀጥታ የተያያዙ ጉዳዮች ሆኑ፡፡

እግዚአብሔር ለሥራ ያለው አጠቃላይ መርህ ከተረዳን ከውድቀት በኋላም ሐሳቡ አልተቀየረም፡፡ ከውድቀት የተነሣ ግን የሰው ልጆች አስተሳሰብ እጅጉን ተዛብቷል፡፡ ማጭበርበር፣ ማበላሸት፣ ስግብግብነት ወዘተ… የሚባሉ የኃጢአት ውጤቶች የሰውን አስተሳሰብ በክለውታል፡፡ ኃጢአት በሰውና በእግዚአብሔር ብቻ ሳይሆን በሰውና በፍጥረት መካከልም ችግር ፈጥሯል፡፡ አንደኛ ምድር እንደ ቀድሞ ፍሬያማ መሆን አልቻለችም፡፡ “እሾህንና አሜከላን ታበቅልብሃለች” የተባለች ምድር ብዙ የምታስለፋ ትንሽ የምትሰጥ ሆነች ፡፡ ሰውም ምድርን ከመንከባከብ ይልቅ ወደ መበዝበዝ ሄደ፡፡ ዛሬ በዓለም ላይ የተፈጠረው የአየር ንብረት መዛባት የዚህ ዝግብግብነትና ለፍጥረት ግድ የለሽ መሆን የፈጠረው ጦስ ነው፡፡

ሥራ ከክርስቶስ ቤዛነት በኋላ

ጻድቅ ሰው ለእንስሳው ነፍስ ይራራል፤ የኀጥኣን ምሕረት ግን ጨካኝ ነው።

መጽሐፈ ምሳሌ 12፡10

የክርስቶስ የቤዛነት ሥራ በዋናነት በአዳም ኃጢአት ምክንያት ከገነት የተባረረውን ሰው ወደ ቀድሞ ንጽህናው በመመለስ ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ ከፈተጥሮ ይልቅ የሰው ልጅ ላይ ነው የሠራው። ምክንያቱም የዚህ ዓለም ቀውስ ዋና ምክንያቱ የሰው ልጅ ራሱ ስለሆነ የሰው አስተሳሰብ ሲታደስ ፍጥረት አብሮ ይታደሳል፡፡ የፍጥረት በሽታ ሰው ነው፣ መድኀኒቱም ሰው ነው፡፡

ብዙውን ጊዜ የምታዘበውን አንድ ጉዳይ እዚህ ጋር ባነሳ ሀሳቤን የበለጠ ግልጽ ያደርግልኛል፡፡ እኔ የምኖርበት ግቢ ውስጥ ከርከሮዎች ይኖራሉ፡፡ ከርከሮዎች ሰውን የሚተኗኮሉ እንስሳት አይደሉም፣ ሣር ይበላሉ፣ አንዳንዴም ከሰው የተረፈውን ፍርፋሪ ይበላሉ፡፡ ታዲያ እነዚያ እንስሳት ባጠገባችን በሚያልፉበት ጊዜ ሁሉም ሰው ማለት በሚቻል ደረጃ ድንጋይ አንስተው በላያቸው ላይ እንደ ናዳ ማውረድን ይወዳሉ፡፡ ለምን እንደሚወግሯቸው ለብዙ ጊዜ አልተገለጠልኝም ነበር፡፡ ከብዙ ማብሰልሰል በኋላ እኔም ድሮ ልጅ እያለሁ ወፍና እንሽላልቶችን እንደምገድል ትዝ አለኝ፡፡ ለካስ እኔም የእንስሳት ገዳይ ነበርኩ፡፡ ትዝ የሚለኝ ወፎችን የምንገድለው ለጫወታ ነው፣ እንሽላልቶችም እንደዚሁ፡፡ እኛም እንደ ልጆች ይህንን ባህሪ ከማኅበረሰቡ ነው የወረስነው፡፡ ምንም የማይተኗኮሉ፣ እህል የማያወድሙ፣ የቤት እንስሳትን የማይበሉ እንስሳት ቢሆኑ እንኳን እንዲሁ መግደል ያስደስታል፡፡ አሁን ሳስበው ግን በውድቀት ምክንያት የመጣ የተበላሸ አስተሳሰብ መሆኑን እረዳለሁ፡፡ የሰው ልጅ ከፈጣሪው ጋር ብቻ ሳይሆን ከፍጥረት ጋርም ጠብ ውስጥ ገብቷል፡፡ አንዳንድ እንስሳትም የሰው ልጅን በመናደፍ፣ በመናከስና ምቾት በመንሳት አጸፋውን ሲመልሱ እናያለን፡፡

የሰው ልጅ ግን ፍጥረትን እንዲንከባከብ እንጂ አላግባብ እንዲያንገላታቸው አልነበረም፡፡ ዛሬ የዓለም ኃያላን መንግሥታት የመወያያ አጀንዳ ከሆኑ ርዕሶች መካከል አንዱና ዋንኛው የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ነው፡፡ የደን ጭፍጨፋ፣ በካይ ጋዞችን ወደ አየር መልቀቅ፣ ከከተማ የሚወጡ መርዛማ ፍሳሽ ወዘተ… በተፈጥሮ ላይ ብዙ ለውጦችን አምጥቷል፡፡ ኦዞን የተባለው አየር መሸንቆር፣ የበረዶ ግግሮች መፍረስ፣ የደን መራቆት፣ የዓለም ሙቀት መጨመረ… ወዘተ ዓለምን እያስፈራሩ ያሉ ሰሞንኛ አጀንዳዎች ናቸው ፡፡ ይንን ነገር ለመቀነስ ስብሰባዎች ቢካሄዱም ብዙውን ጊዜ ስብሰባዎቻቸው ያለ ስምምነት ይጠናቀቃሉ፣ ቢስማሙ እንኳን እናደርጋለን ያሉትን ሲተገብሩ አናይም፡፡

የክርስቶስ የቤዛነት ሥራ አዳም ከውድቀት በፊት ወደ ነበረበት ደረጃ መመለስ ነው፡፡ ሆኖም ግን የሰው ልጅ አሁን ኃጢአት የመሥራት ዝንባሌ ስላለው ብዙውን ጊዜ ወደ ኋላ እየተንሸራተተ ወደ ነበረበት የኃጢአት ዓለም ሲመላለስ ይስተዋላል፡፡ የሥራ ባህልም ከዚህ አንጻር የሚታይ ይሆናል፡፡ በውድቀት ዘመን ሲያደርጋቸው የነበሩ ዝግብግብነት (ለኔ ብቻ ማለት) ፣ ማምታታት፣ ሳይሠሩ መብላት መፈለግ፣ መለገም፣ ስንፍና፣ ማጭበርበር ወዘተ… የተጣቡ ባህሪያት ናቸው፡፡ ሆኖም ግን እነዚህ ባህሪያት በክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር የሚፈቀዱ አልነበሩም፡፡ በተዋጀው ጤናማ አስተሳሰብ ሥራ ከፈጣሪ የተሰጠን ኃላፊነት ነው፡፡

ሥራ አገልግሎት ነው

ሰው የተፈጠረው እግዚአብሔርን ለማገልገል እንደሆነ ክርስቲና ያስተምራል፡፡ ምናልባት ብዙ ሰው የማይጠይቀው ወይም ጠይቆም ያልተረዳው ‹እግዚአብሔርን እንዴት እናገልግል› የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ ብዙ ሰዎች አገልግሎት የሚመስላቸው በቤተ አምለኮዎች ውስጥ የሆኑ ተግባራት ላይ መሳተፍ ብቻ ሊመስላቸው ይችላል፡፡ አንድ ሰው እግዚአብሔርን እያገለገለ ነው የሚባለው በቤተ ክርስቲያን አካባቢ የሆነ ሥራ ሲሠራ ወይም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ‹መንፈሳዊ› ተብለው የተመደቡ ሥራዎች ላይ የተሠማራ እንደሆነ ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ሥራን ‹‹ዓለማዊና ሥጋዊ›› ብሎ የሚፈርጅ ምንታዌ አስተሳሰብ አለና፡፡ ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱሰ የሥጋ ሥራዎች ብሎ የሚዘረዝራቸው የሥነ ምግባር ግድፈቶችን እንጂ ራሳችንን ለመመገብ የምንሠራው ሥራ አይደለም፡፡

አገልግሎት ለፈጣሪ መኖር ነው

 የፈጠረን አምላክ አለ ብለን ካመንን ለምን ዓላማ እንደፈጠረን መጠየቁ ተገቢ ነው፡፡ ይኸ ነው የሕይወት ትርጉም ፍለጋ ማለት፡፡ እንዲሁ በልተን ጠጥተን፣ አደገን ተመንድገን፣ በዝተን ተባዝነት… እንድንሞት ነው? ይህ የኪሳራ ሕይወት አይደለምን? እግዚአብሔር ሲፈጠረን እኛን ለፈጠረበት ዓላማ እንድንኖር ነው ከኛ የሚጠብቀው፡፡ በዋናነት ግን እሱን እንድንታዘዝ ነው፡፡

አገልግሎት ሰውን ማገልገል ነው

ከአጥር ውዲህ ተከማችተን
ጭፍራ ዝላዩን ትተን
እስቲ እንውጣ ከአዳራሹ
ፍቅር ድጋፍ ወደሚሹ[1]

ከፍጥረታት ሁሉ መሃለ በአምላኩ መልክና አምሳል የተፈጠረው የሰው ልጅ ብቻ ነው፡፡ ለዚህ ነው የሰው ልጅ `ክቡር ነው` የሚባለው፡፡ የዚህ ዓለም ያለው ማንኛውም ነገር በሰው ልጅ ዙሪያ ነው የሚያጠነጥነው፡፡ ስለዚህ ስለ አገልግሎት ስናሰብ የሰው ልጅ ማዕከላዊ ሥፍራ ይይዛል ማለት ነው። በሌላ አነጋገር ፈጣሪን ማገልገል ራሱ ለሰው ልጅ ከምናደርገው ነገር ጋር ይያያዛል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ሰዎች በፍየሎችና በጎች ተመስለው በሠሩት ሥራቸው ከፈጣሪያቸው ዋጋቸውን ሲቀበሉ የሚያብራራ ክፍል አለ፡፡ በጎች ለተባለሉት፡-

ተርቤ አብልታችሁኛልና፥ ተጠምቼ አጠጥታችሁኛልና፥ እንግዳ ሆኜ ተቀብላችሁኛልና፥ ታርዤ አልብሳችሁኛልና፥ ታምሜ ጠይቃችሁኛልና፥ ታስሬ ወደ እኔ መጥታችኋልና።

በዚህ አባባሉ ግራ የተጋቡ በበጎች የተመሰሉ ጻድቃን፡

ጌታ ሆይ፥ ተርበህ አይተን መቼ አበላንህ? ወይስ ተጠምተህ አይተን መቼ አጠጣንህ? እንግዳ ሆነህስ አይተን መቼ ተቀበልንህ? ወይስ ታርዘህ አይተን መቼ አለበስንህ? ወይስ ታመህ ወይስ ታስረህ አይተን መቼ ወደ አንተ መጣን?

እሱም ሲመልስ፡-

እውነት እላችኋለሁ፥ ከሁሉ ከሚያንሱ ከእነዚህ ወንድሞቼ ለአንዱ እንኳ ስላደረጋችሁት ለእኔ አደረጋችሁት ይላቸዋል።

የማቴዎች ወንጌል 25፡35-40

በተቃራኒ ይህንን ተግባር ያላደረጉ በፍየል የተመሰሉ ሰዎች ከፈጣሪያቸው ውግዘትን ሲቀበሉ እናነባለን፡፡ ስለዚህ ሰውን ስናገለግል የፈጠረንን አምላክ እንደምናገለግል መዘንጋት የለበትም፡፡ ሌላው ቀርቶ የእግዚአብሔር ልጅ የሆነው ኢየሱስ በዚህ ምድር ላይ በተመላለሰበት ዘመን ዓላመው የሰውን ልጅ ማገልገል እንደሆነ በግልጽ አስቀምጧል፡፡

እንዲሁም የሰው ልጅ ሊያገለግል ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም። የማቴዎስ ወንጌል 20፡28

የሰው ልጅ (ኢየሱስ) ማንን ለማገልገል ነው የመጣው ያልን እንደሆነ ‹‹የሰውን ልጅ›› ነው ምላሻቸን፡፡ ነፍሱን እንኳን ሳይቀር ለብዙዎች ቤዛ ለማድረግ የመጣው ለሰው ልጅ ብሎ ነው፡፡

ስለዚህ በክርስቲና ሃይማኖት ማዕቀፍ ውስጥ ያሉ ሰዎች የአገልግሎት እሳቤያቸን ከዚህ አንፃር ሊቃኙ የተገባ ነው፡፡ በየመስሪያ ቤቶች ተቀጥረን ወይም የራሳችን ንግድ ከፍተን የምንሠራ ሰዎች ሥራውን ደሞዝ ለማግኘት ወይም ትርፍ ለመሰብሰብ ብቻ አድርገን ካሰብነው ከእውነተኛ ተልዕኳችን ጋር እንጋጫለን፡፡ ሥራል ከገቢ ማስገኛ በላይ የሕይወታችን ግብ ወይም ጥሪ የምናሳካበት መንገድ ነው አምናለሁ።

ምናልባትም ዛሬ የምንመለከተው የተገልጋዮች መጉላላት ምንጩ ምን እንደሆነ ብንመረምር እያንዳንዱ አገልገሎት ሰጪ ግለሰብ ሥራው ባግባቡ ስላልተወጣ ሊሆን እንደሚችል መገመት አይደከብድም፡፡ መንግሥት ሠራተኛው ሥራው ደሞዝ ከመብላት ባለፈ ፈጣሪውን እንደሚያገለግል ከተረዳ የተጣለበትን ኃላፊነት በአግባቡ ስለሚወጣ ብዙ ለውጥ እንደሚመጣ እሙን ነው፡፡ ነጋዴውም በተመሳሳይ መልኩ ትርፍ ከማጋበስ አልፎ የተሰጠው የአገልገሎት አደራ መሆኑን ከተረዳ አላግባብ ዋጋ መጨመር፣ ማጨበርበርና ከመንግሥት ጋር የግብር ድበቃ ድብብቆሽ ጫወታ ውስጥ ላይገባ ይችላል፡፡


[1] ዘማሪ ደረጀ ከበደ (ዶ/ር) ቁጥር ፡ የአድናቆት ቀን ለእግዚአብሔር አልበም

Avatar

By Guwad K.

Kaftle Torayto is a graduate of computer Science and Information Technology from Arbaminch Univeristy. His passion is writing, reading, listening music, graphics design and network engineering. Now days, he is working in Arbaminch Mekane Yesus Technical College.

Related Post

6 thoughts on “እውነተኛ የሥራ ግንዛቤ በክርስቲና ክፍል ፮”
  1. May God bless you! this topic is secured from all of us because we focus on events which happen around as rather than why we are existed in this world. But the plan of God is not to fixes our eyes on dramatically fecks or we are not created without purpose and visions to establish. Be continue peales i know you have very amazing understand why God created human being but we are yet not discover you put your legacy.

  2. በታም ደስ ይላል ተባረክ!!! ስለ ህይወትም ሆነ ስለ እውቀት ብዙ ትምህርቶቹን አግንቻለሁኝ Thank you bro

  3. ስለ ሕይወትም ሆነ ስለ ትምህርተታወዊ በቂ እውቀት አግንቻለሁኝ ተባረክ!!! በታም እንወድሀለን Bro

  4. May the God of Heaven bless you. It is a very life-changing lesson. It is a building lesson that changes the direction from where we are in the beginning. Bless you my brother.

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *