ለመሆኑ የምንማረው ለምንድን ነው?

Avatar By Guwad K. Apr 3, 2024

እጓለ ገብረ ዮሐንስ (ዶ/ር) የተባለ ሊቅ “የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ” በሚለው ድንቅ መጽሐፋቸው ትምህርት ሦስት ዓላማዎች እንዳሉት ያብራራሉ። አንደኛው በትምህርት አማካይነት ወደ ሰው ደረጃ ለመድረስ ነው። ይህ ሲባል ሰው የሚማረው ከዝቅተኛው ከእንስሶች ጋር የጋራ ከሆነው ሥነ-ፍጥረታዊ ሁኔታ ወጥቶ በሐሳቡ በምኞቱ ሥዕል መሠረት ከከፍተኝነት ከሙሉ የሰውነት ደረጃ ለመድረስ ነው[1]።  በዚህ መሠረት ትምህርትን የጥቅም ማግኛ አቋራጭ መንገድ አድርገው የሚያስቡ ሰዎች የትምህርት ዓላማ ጋር የተላለፉ ናቸው ማለት ነው። ዕውቀት ሲጨምር ሰው እንስሳዊ ፍላጎቶችን እየገታ ከፍ ወዳሉ ሰብአዊ እሳቤዎች ያድጋል ማለት ነው። እንደ እጓለ ገብረ ዮሐንስ አገላለጽ በሰው ውስጥ ሁለት ኀይላት ይገኛሉ። አንደኛው ኀይል ወደ ላይ ወደ ከፍተኛ የመለኮት ባህሪይ የሚጎትት ሲሆን ሌላኛው ወደ ታች ወደ ዝቅተኝነት ማለትም ሥጋዊ ተድላዎችን ወደ ማሳደድ ይጎትታል ማለት ነው። በነዚህ ሁለት የፍላጎት ጉተታዎች ምክንያት ሰው ውስጥ ከባድ ትግል ይካሄዳል ማለት ነው።

የትምህርት ዓላማ ይህ ነው፣ ሰውን ከዚህ ጭንቅ ነጻ ማውጣት፣ በኅሊናው ብርታት ሁለቱ ፈረሶች ሠረገላውን በተቃራኒ አቅጣጫዎች መሣባቸው በገራምነት ወደ ላይ ወደ ከፍተኛነት የሚያደርሰውን አቅጣጫ መርጠው ሰውን ወደ መቅደማዊው ምንጭ ወደ መለኮት እንዲያደርሱት አስፈላጊ ነው[2]

ሁለተኛ የትምህርት ዓላማ መክሊት መፈለጊያ መሣሪያ ነው። ይህ ማለት እያንዳንዱ ሰው ሲፈጠር እንደ ሌሎች እንስሳት ተፍጥሮአዊ ሂደቶች ማለትም መወለድ፣ መብላት፣ ማደገ፣ መውለድ፣ ማርጀትና መሞት ብቻ የሚያልፍ ሳይሆን የተፈጠረበትን ምክንያት የሚፈልግና እስከሚያገኘው ደርስ ብዙ የሚባዝን ፍጥረት ነው።

የነገር ሰብዕ ምርመራ ሊቃውንት እንደሚናገሩት ሰው ከዘሩ የሚውርሳቸው ወይም በከፊል በአባት በእናት ሳይኖሩ በልጅ ብቻ የሚገኙ ኔቸር(Nature) ባልታወቀው ምሥጢራዊ ጥበብ ያስቀመጠቻቸው ሀብታት አሉ[3]። ትልቁ የሕይወት ትግል በውስጣችን በምሥጢር የተቀመጠውን ሀብት ፈልጎ ማግኘትና ለዚያ መኖር መቻል ነው። ትምህርት ለዚህ አጋዥ መሣሪያ ነው። ስለዚህ ሰው የሚማረው ዝንባሌውን ወይም የተሰጠውን መክሊት ለመለየትና በዕውቀት ጐትጒቱ ለማሳደግ ነው ማለት ነው።

ሦስተኛ የትምህርት ዓላማ አዲስ ነገር ከማወቅ ከመመራመር የእስካሁኑ የዕውቀት ድንበር አልፎ ለመሄድ ከመጣጣር ጋር የተያያዘ ነው። ሰዎች ምድር የሚቆፈሩት፣ ባህር ጠልቀው የሚገቡት፣ ወደ ሰማይ አንጋጥጠው የሚመለከቱት ጥልቅ የማወቅ ፍቅር ስላላቸው ነው። ይህንን በማድረጋቸው ብዙ ግኝቶችን አስገኝተዋል። ከምንኖርበት ዓለም ውጪ ሌሎች ብዙ ዓለማት መኖራቸውን ብቻ ሳይሆን ወደዚያ ለመፍለስ እስከ መዘጋጀት ደርሰዋል። ይህ የዕውቀት ኀይል የሚያደረገው ነው። ስለዚህ ሰው የሚማረው ወይ ቀደምት ምሁራን ያገኙትን ነባር ዕውቀት የግሉ ለማድረግ፣ ከተቻለም አዲስ ነገር አስሶ ለማግኘት እንጂ አሁን በአገራችን አውድ እንደሚባለው ለመብላት አይደለም። ለመብላት መማር አያስፈልግም፣ የሰማይ አእዋፋት፣ የምድር እንስሳት ከበሉ ባለ ምጡቅ እአምሮ ባለቤት የሆነው የሰው ልጅ እንዴት ለመብላት ብሎ ዓመታትን ይፈጃል?

ትርጉም ፍለጋ

ለምንኖረው ሕይወትና በየቀኑ የምንወስናቸው ውሳኔዎችና የምንመርጣቸው ምርጫዎች በቀጥታ ለሕይወት ከምንሰጠው ትርጉም ጋር የተያያዘ ነው፡፡ እኔ ማን ነኝ? ከየት ነው የመጣሁት? ወደዚህ ዓለም የመጣሁት የትኛውን ተልዕኮ ለመፈጸም ነው? ሕይወትስ ትርጉም አላት? ወይስ እንዲሁ እየኖሩ መቀጠል ነው? ወዘተ… የሚሉ ጥያቄዎች ለዘመናት የሰውን ልጅ ሲያመራምሩ የኖሩ ግና ደግሞ ሁሉንም የሚያረካ ምላሽ ባለማግኘታቸው ዛሬ ድረስ የሚጠየቁ ናቸው፡፡ አሥሬ ተጠይቆ፣ አሥሬ ምላሽ ተሰጥቶበት አሁንም አሥሬ የሚጠየቁ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ጥያቄዎች በብዛት ከሰው ልጅ ዕድገት ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ የሰው ልጅ ፍላጎት ከመሠረታዊ ጉዳዮች ከፍ ብሎ እራሱንና አካባቢውን ለማወቅ በሚጀምርበት ጊዜ ከእንደዚህ ዓይነት ጥያቄዎች ጋር ያፋጠጣል፡፡

የሕይወት ትርጉም ምንድን ነው?

እስከ መካከለኛው ዘመን ድረስ የነበረው የሰው ልጅ የንጽረተ ዓለም ምንጭ ሃይማኖት ነበር፡፡ አብዛኞች የሕይወት ጥያቄዎች ምላሻቸውን የሚያገኙት ከሞላ ጎደል ከሚከተሉት የሃይማኖት አስተምህሮዎች ነው ማለት ይቻላል፡፡ የሕይወት ትርጉም ጥያቄም ከቅዱሳት መጽሐፍት በተቀዱ አስተምሀሮች ከሚመነጭ ትንታኔ ላይ የተመሠረተ ነበር፡፡ የሰው ልጅ ህልውና በቀጥታ ከእግዚአብሔር ዓላማ ጋር የተያያዘ ነበር፡፡

ሆኖም ከጊዜ በኋላ የሰው ልጅ ሃይማኖትን እንደ እስራት በመቁጠር ‹‹እራሴን ነፃ አወጣለሁ›› ብሎ ሌሎች አማራጮችን ማማተር ተያያዘው፡፡ በተለይ የ18ኛ እስከ 20ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ ያሉት ዘመናት በዚህ ይታወቃሉ፡፡ ዘመነ አብርሆት ተብሎ የሚጠራው የ18ኛው ክፍለ ዘመን የሚታወቀው ሃይማኖት፣ ባህልና ትውፊት ላይ በመዝመት ነበር፡፡ በእነዚህ ማኅበራዊ እሴቶች ፈንታ አመክንዮ፣ ምክንያትና ሳይንስ ተተካ፡፡ የሰው ልጅ ጥያቄ ሙሉ በሙሉ ይመልሳሉ ተብለው ተስፋ ተጣለባቸው፡፡ በእነዚያ ዘመናት ለሕይወት ትርጉም ለመስጠት ተብሎ እንደ አማራጭ ከቀረቡ ሀሳቦች መካከል Existentialism, Nihilism Absurdism የተሰኙ የፍልስፊና አስተሳሰቦች ይገኙባቸዋል፡፡

Existentialism ‹‹የሰው ልጅ ግንዛቤውን በመጨመር፣ ነፃ ፈቃዱን በመጠቀምና ግላዊ ኃላፊነቱን በመወጣት በዚህ ትርጉም በሌለው ዓለም የራሱን ትርጉም ሊፈጥር ይችላል›› የሚል አስተሳሰብ ነው፡፡

Nihilism ‹‹ዓለም ትርጉም አልባ ብቻ ሳትሆን `ትርጉም አገኛለሁ` ብሎ ፍለጋ መውጣት በራሱ ትርጉም የለሽ ልፋት ነው›› የሚል አውዳሚ ፍልስፊና ነው፡፡

Absurdism በበኩሉ የሰው ልጅ ትርጉም አልባና ቀውስ በሞላት ዓለም ውስጥ የተጣለ ምስኪን ፍጡር ቢሆንም ትርጉም ፈለጋውን ግን አያቆምም፡፡ የሌለውን ትርጉም ፍለጋና የተፈለገው ትርጉም አለመገኘት ምክንያት የሚፈጠር ቀውስ ላይ ያተኩራል፡፡ ስለዚህ ሰው ማድረግ ያለበት ሦስት ነገሮች አሉ ይላል የAbsurdism ፍልስፍና ተከታዮች፡፡ 1ኛ “Philosophical Suicide” መፈጸም ነው፡፡ Philosophical Suicide የፍልስፊና ሕይወቱን ትቶ የሕይወት ትርጉሙን ከሃይማኖት አስተምህሮዎች መፈለግን መጀመር እንደ ማለት ነው፡፡ 2ኛ፡ “Physical Suicide” ወይም በእውነት ራስን ማጥፋት ነው፡፡ ወደ ሃይማኖት አልመለስ የሚል ከሆነ፣ ነገር ግን ደግሞ ለሕይወቱ ትርጉም ማግኘት ካልቻለ ያለው አማራጭ እራስን ማጥፋት ብቻ ነው፡፡ 3ኛ፡ “Acceptance” ወይም ሕይወት ትርጉም እንደሌላት አምኖ መቀበልና ፍለጋ አለመኳተን ማለት ነው፡፡ የሰው ልጅ ሕይወት ትርጉም የላትም ብሎ ዝም ብሎ ቁጭ እንዲል ሳይሆን ለሱ የሚሆን ትርጉም በራሱ ፈጥሮ እንዲኖር ይመክራሉ፡፡

 ደረጃቸው ይለያያል እንጂ ሁሉም አስተሳሰቦች ‹‹ሕይወት ትርጉም አልባ ነች›› የሚሉ ናቸው፡፡ ይህ የሕይወት ትርጉም ፈለጋ ከፈጣሪ ውጪ የሚደረግ ጥረት ነው፡፡ ዓለምንና በውስጧ ያሉትን የፈጠረ አምልክ ከሌለ፣ ዓለም እንዲሁ በዘፈቀደ ድንገት የመጣች ከሆነ ትርጉም የሚባለ ነገር አይኖርም ማለት ነው፡፡ በተቃራኒው ዓለም በፈጣሪ የተፈጠረች ነው ብለው የሚያምኑት የትኛውም ፍጥረት ያለ ትርጉም እንዳልተፈጠረ ይረዳሉ፡፡

ከጊዜ በኋላ ግን ያለ `ሕይወት ትርጉም` መኖር እንደማይቻል አሊያም ኑሮን አዳጋች እንደሚያደርግ ጥናቶች አረጋግጠዋል፡፡ በተለይ ከናዚ ምድራዊ ገሃነም ተርፎ የወጣው ኦስትሪያዊ ሳይካትሪስት ቪክቶር ፍራንክል የሰው ልጅ ያለ ሕይወት ትርጉም መኖር እንደማይችል እዚያ ኮንሴንትረሽን (concentration camp)[4] ካምፕ ውስጥ በነበረ ጊዜ አረጋግጧል፡፡ እዚያ በሞት ቀጠና ውስጥ በብዙ ስቃይ ውስጥ በነበሩ ጊዜ የተለያዩ በሽታዎችን ልመቋቋምና እስከ መጨረሻው ድረስ ለመኖር እየታገሉ የቆዩት በሕይወታቸው አንዳች ትርጉም ሰጥተው ለዚያች ትርጉም ሲሉ የሚኖሩ ሰዎች እንደሆኑ ያብራራል፡፡ ተስፋ የቆረጡ፣ ‹‹ለምንድን ነው የምኖረው? ›› ለሚለው ጥያቄ በቂ ምላሽ መስጠት የማይችሉ ሰዎች ወዲያው በታይፈስ ይሞታሉ፣ አሊያም የናዚ ወታደሮች ወደሚንቀለቀለው እቶን ይወረውሯቸዋል፣ ምክንያቱም ሰዎች ተስፋ በመቊረጥ ምክንያት ደክመው ለሥራ ስለማይበቁ፡፡

ይህ ምሁር ሎጎቴራፒ የሚባል አዲስ የሕክምና ዘዴም ለዓለም አስተዋውቋል፡፡ ሎጎቴራፒ ሰዎች በሕይወታቸው ትርጉም እንዲያገኙና ለዚያች ትርጉም ብለው እንዲኖሩ የሚረዳ የሕክምና ዘርፍ ነው፡፡ ሎጎቴራፒ ነገ ላይ ነው የሚያተኩረው፣ ወደፊት በታካሚው በሚሳኩ የሕይወት ገቦች ላይ[5]፡፡ እንደምናውቀው ሕይወት በብዙ እንቆቅልሾችና ትግሎች የተሞላች ነች፡፡ በእያንዳንዱ የሕይወት እርምጃዎቻችን ላይ ፈተና ይገጥመናል፡፡ እነዚያን የሕይወት ፈተናዎችና መሰናክሎች ማለፍ የምንችለው በሕይወታችን ‹‹እናሳካለን›› ብለን የምናልመው ግብ ሲኖር ብቻ ነው፡፡ ሎጎቴራፒ ለሰዎች ‹‹ለምን›› የሚለውን የሕይወት ግብ መስጠት ላይ ያተኩል፡፡ ሰዎች የሚኖሩለት ከዚያም አልፎ የሚሞቱለት “ለምን” ካላችው እንዴት መኖር እንዳለባቸው ያውቃሉ፡፡

አንድ ወቅት ላይ ዶክተር ማይለስ ሙንሮ የተናገረ ነው ተብሎ ፌስቡክ ላይ የተለጠፈ ጽሑፍ አንብቤ ነበር፡፡ ጽሑፍን ካነበብኩ ትንሽ ቆየት ስላለ ቃል በቃል ባላስታውስም ሐሳቡ ግን እንዲህ የሚል ነበር፡-

‹‹ብዙ መጽሐፍትን ጽፍያለሁ፣ ብዙ ሰዎችን አሠልጠኛለሁ፣ ዓለም ሁሉ ላይ ዞሬ ንግግሮችን አድርግያለሁ… አሁን ግን ባዶነት ይሰማኛል፡፡ መስጠት ያለብኝን ሁሉ ስለ ሰጠሁ ከዚህ በኋላ ለዓለም የሚሰጠው ነገር የለኝም፡፡”

ዶ/ር ማይለስ ይህንን በተናገረ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከሚስቱ ጋር በአይሮፕላን አደጋ ሕይወቱ አልፏል፡፡ ዶ/ር ሩጫውን ጨርሷል፣ ዝም ብሎ ምድር ላይ ረጅም ዕድሜ መኖር ቁም ነገር አይደለምና፡፡ ዶ/ር ማይለስ ራሱ የሕይወት አሳዛኝ ገጽታ (ትራጀዲ) ሞት ሳይሆን ያለ ግብ ወይም ዓላማ መኖር ነው ብሎ አስተምሯል፡፡

The greatest tragedy in life is not death, but life without a purpose[6].

ሰዎች ሞትን ይፈሩታል፣ ግን ሞት ሳይሆን መፍራት ያለብን ለምን እንደምንኖር ያላወቅን እንደሆነ ነው፡፡

በኛ አገር አውድ

በዛሬው ዓለም እጅግ አሳሳቢ ከሆኑ ችግሮች መካከል አንዱ ጭንቀት ነው፡፡ በተለይ በሠለጠነው ዓለም ሰዎች ብዙውን ጊዜ ለድባተና ከፍተኛ ለሆነ የአእምሮ ቀውስ ይዳረጋሉ፡፡ አብዛኞቹ የጭንቀቱ ምንጭ ከሕይወት ትርጉም ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ሰዎች ለምን እንደሚኖሩ በወጉ ካላወቁ በቀላሉ ለጭንቀት ይዳረጋሉ፡፡

በኛ አገር አውድ ስንወስድ ግን የምንጨነቅባቸው ምክንያቶች ግን ከሕይወት ትርጉም ጋር በተያያዘ ሳይሆን በዕለት ዕለት ሕይወት ከሚገጥሙን ችግሮችና በብዛት የኢኮኖሚ ችግሮች ጋር የተያያዘ እንደሆነ አስባለሁ (በዚህ ጉዳይ ላይ የተሠራ ጥናት መኖሩን እንጃ) ፡፡ ብዙ ኢትዮጵያውያን የሕይወት ትርጉም ሲያሳስባቸው ወይም ‹‹ለምንድን ነው የምኖረው? ›› ብለው ሲጠይቁ አይሰማም፡፡ ወይም ደግሞ ለውስብስብ የሕይወት ጥያቄዎች ቀለል ያሉ ምላሾችን መስጠት የተለመደ ነው፡፡

እንደ ምዕራቡ ዓለም ከልክ ባለፈ ጭንቀት እራስን ማሰቃየትም ሆነ ስለ ሕይወት ምንም ዓይነት ጥያቄ አለማቅረብም ሁለቱም እኩል አደገኞች ናቸው ብዬ አስባለሁ፡፡ በአስተሳሰብ ለውጥ ወይም አእምሮ ዕድገት ምክንያት የሚከሰት የሕይወት ጥያቄ ብዙ ሰዎችን በመካከለኛ ዕድሜያቸው እንደሚጎበኛቸው ይነገራል፡፡ ይህ የሕልውና ጥያቄ በቂ ምላሽ ካላገኘ ወደ ከፋ የአእምሮ መታወክ ይመራል፡፡ ከዚህ የተነሣ ብዙዎች ራሳቸውን እስከማጥፋት ይደርሳሉ፡፡ የኛ አገር ግን ለጥያቄ ብዙ ቦታ ስለማይሰጥ ወይም እንደዚህ ዓይነት የኅልውና ጥያቄ ማቅረብ ስለማያበረታታ ሰዎች ጥያቄያቸውን ባደባባይ ስገልጹ አይታይም፡፡

የሕይወትን ትርጉም በወጉ አለማወቅ ደግሞ ሰዎች በተራ ጉዳዮች ብቻ ላይ እንዲያተኩሩ ያደርጋቸዋል፡፡ ከመሠረታዊ ፍላጎቶች ውጪ ከፍ ያለ ነገር እንዳያስቡ እንዳይመራመሩ ያግዳቸዋል፡፡ የማይጠይቁ፣ የማይመራመሩና ለምን እንደሚኖሩ የማይረዱ ሰዎች የበዙበት ማኅበረሰብ ብዙ ለውጥ አይመጣም፡፡ እንደ እንስሳ በልቶ ማደር የሕይወት ግብ ይሆናል።

እርግጥ ነው ድህነታችን መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ብቻ ትኩረት እንድናደርግና የሕይወትን መሠረታዊ ጥያቄዎች ወደ ጎን እንድንተው አድርጎናል፡፡ ነገር ግን ለውጥ እንዲመጣና ከራሳቸው አልፈው ለትውልድ የሚበቃ ነገር ማበርከት የሚችሉ ግለሰቦች እንዲፈጠሩ ሰዎች ከመሠታዊ ነገሮች በላይ ማሰብ እንዲችሉ ማነሳሳት ተገቢ ነው፡፡ እያንዳንዱ ሰው ‹‹ለምኑን›› ማግኘት ይኖርበታል፡፡ ለምን እንደሚኖር የሕይወቱን ግብ/ዓላማ ካገኘ በሚሠራው ሥራ ውጤታማ መሆን ይጀምራል፡፡

ትርጉም ሲባል

ትርጉም ሲባል የግድ እንደ ኒል አርምስትሮንግ ጨረቃ ላይ መውጣት ማለት ላይሆን ይችላል፣ እንዴ አልበርት ኢንሰታይንም ሕዋን የሚያስቃኝ ኀልዮት(Theory) መቀመርም ላይሆንም ይችላል፡፡ እያንዳንዱ ሰው በተሰጠው ልክ ነው መኖር ያለበት፡፡ ወይም እያንዳንዱ ሰው በእጁ ባለው ሥራ ለውጤታማነት ሊታገል ይገባል ለማለት ነው፡፡

ለምሳሌ አንድ የጤና ባለሙያ የሕይወት ትርጉም ማሳካት ያለበት ለታካሚዎች በሚያደርገው እንክብካቤ ነው፡፡ የሱ ተልዕኮ የበሽተኞችን ጤና መመለስ ነው፡፡ ሥራውን እንደ ሕይወቱ ተልዕኮ ማየት ይኖርበታል፡፡

አንድ የግብርና ባለሙያም እንደዚሁ የአርሶ አደሮችን ሕይወት የሚቀይር ተጽዕኖ መፍጠር ከቻለ የሕይወቱን ግብ መፈጸም ችሏል ማለት ነው፡፡

ከዚህ ጋር የተያያዘ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ አለ፡፡

ወደ ሌላ አገር የሚሄድ ሰው ባሮቹን ጠርቶ ያለውን ገንዘብ እንደ ሰጣቸው እንዲሁ ይሆናልና፤ ለእያንዳንዱ እንደ ዓቅሙ፥ ለአንዱ አምስት መክሊት ለአንዱ ሁለት ለአንዱም አንድ ሰጠና ወደ ሌላ አገር ወዲያው ሄደ።

ማቴዎስ ወንጌል 25፡14-15

እያንዳንዱ አገልጋይ የተቀበለውን መክሊት ተቀብሎ ነግዶ ሲያተርፍ አንደኛው ግን ወሰዶ ቀበረው፡፡ ጌታቸው በመጣ ጊዜ ሁሉም የሠሩትን ርፖርት አቀረቡ፣ ያተረፈው ሲሸለም የቀበረው ግን ቅጣት ሲጣልበት እናያለን፡፡ ይህንን ሐሳብ መንፈሳዊ ከምንላቸው ሥራዎች ብቻ መወሰኑን ትተን በተሰማራንባቸው ሥራዎች ሁሉ ተጋባራዊ ብናደርግ የሚሠራ ሕግ ይመስለኛል። ዛሬ የተቀጠርንበት የሥራ መስክ መክሊታችን እንደሆነ ማን ያውቃል! ነገ ከፈጣሪ የሚሰጠን ሽልማት ወይም ቅጣት ከዚህ ሥራ ጋር በተያያዘ የምንፈጽመው ተግባር ቢሆንስ ማን ያውቃል!

ስለዚህ እያንዳንዱ ሰው የተሰጠውን መክሊት እየነገደበት ነው ወይስ ቀብሮታል የሚለው ጥያቄ የሁላችንም አእምሮ ልኮረኩር ይገባል፡፡


[1] እጓለ ገበረ ዮሐንስ፣ ከፍተኛ የትምህርት ዘይቤ (1946 ዓ.ም) ገጽ ፹፮

[2] እጓለ ገብረ ዮሐንስ

[3] ዝኒ ከማሁ

[4] መንግሥትን የሚቃወሙ ሰዎች የሚታሰሩበት ቦታ፣ በተለይ በ፪ኛ የዓለም ጦርነት አይሁዳዊያን የተሰቃዩባቸው እነ ኦሽዊትዝ ያሉ ሥፍራዎችን የሚያመለክት ነው፤

[5]ቪክቶር ኢ ፍራንክል፤ ለምንን ፍለጋ (ትርጉም በቴዎድሮስ አጥላው) 2013 ዓ.ም አዲስ አበባ (ገጽ126)

[6] Myles Munroe: Applying the kingdom (p.13) 2007

Avatar

By Guwad K.

Kaftle Torayto is a graduate of computer Science and Information Technology from Arbaminch Univeristy. His passion is writing, reading, listening music, graphics design and network engineering. Now days, he is working in Arbaminch Mekane Yesus Technical College.

Related Post